ስለ አማራ መደራጀት – ክፍል ፪

በአቻምየለህ ታምሩ፡

አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው እንደ ወያኔና ኦነግ በብሔርተኝነት ስም የኢትዮጵያን ታሪክና የኢትዮጵዊነትን መንፈስ ለማጣጣል አይደለም። አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው ከሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ በገናና ሥልጣኔዋና ታሪኳ በዓለም መድረክ ስሟ ገኖ የወጣውን፣ ከአፍሪካ አልፎ በሰሜን አሜሪካና በካረቢያን በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ተይዘው ሲማቅቁ ለነበሩ ሕዝቦች የነፃነት ምድር፣ የጥቁር ሕዝቦች ተስፋ፣ ‹‹የጥቁር ሕዝቦች የከነዓን ምድር›› በሚል በሰቀቀንና በናፍቆት ሲያስቧትና ሲዘክሯት የኖረችውን ኢትዮጵያን ህልውና ለማጽናት እንጂ እንደ ኦነግና ወያኔ ለመካድ አይደለም።
አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው እንደ ወያኔና ኦነግ በስምና ማንነት ላይ ተመስርቶ የራሱን ወሰንና አጥር ከልሎ ለመኖር፤ ይህና ያ ብሔር በእኔና በዚህ ብሔር ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል፣ ግፍና ጭቆና አድርሶብናል በሚል በሬ ወለደ የጭቆና ታሪክና የተጋድሎ ገድል ለመጻፍና ለማጻፍ፤ በዚያ ላይ ተመስርቶ ለበቀል ለመነሳትና ሌሎችን በጎሪጥ ለማየት አይደለም። አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው ወያኔና ኦነግ እንዳደረጉት በአማራነትና በኢትዮጵያዊነት ላይም ልዩነት ለመፍጠር አይደለም።
አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው እንደ ወያኔና ኦነግ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ የእከሌ ብሔር ወይም ጎሳ በአማራ ላይ ስለፈጸመው በደልና ግፍ ቁም ለማወራረድና ጊዜ እየጠበቀ የሚያመረቅዝ ምሬት፣ ቁጣና የበቀል ሰይፍ ለመምዘዝም አይደለም።
አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው የሐሰት፣ የበቀልና ቂም መምህሮች የሆኑት ወያኔዎች፣ ኦነጋውያንና ተከታዮቻቸው በአማራ ላይ እኩይ የሆነ የበቀል ሒሳባቸውን ለማወራረድና የራሳቸውን መንግስት ለመመስረት ሲሉ ከአማራና ከኢትዮጵያ አንጻር የደረቱትን የፈጠራ ታሪክ ድርሳናትና ገድሎቻቸው እንዲሁም በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያከማቹትን ትናንትና ያልነበረ የቅዠትና ሕልም ተራራ ለመናድ ነው።
እኛ የአማራ ወጣቶች በአማራነታችን የምንደራጀው ማተቡን እንደበጠሰው ያ ትውልድ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በመካድና በማዋረድ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሁሉ የጋራ የነበረውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የነፃነት ተምሳሌት፣ የአንድነትና የፍቅር ኪዳን አድርገን ነው። እኛ የአማራ ወጣቶች በአማራነታችን የምንደራጀው እንደ ኦነግና ወያኔ ፋኖዎች አያቶቻችንን ለማንኳሰስ፣ ታሪካቸውን ለማሳነስ፣ ለነፃነት ያፈሰሱትን ደምና ኢትዮጵያን ለመገንባት የከፈሉትን መሥዋዕትነት ለማራከስ ሳይሆን በኦነግና ወያኔ የቆሸሸውን ያያቶቻችን ክቡር ታሪክና ሕያው አሻራ ከወደቀበት ትቢያ አንስተን ለወደፊቷ አገራችን የሞራልና ወኔ ስንቅ ለማድረግ ነው።
እኛ የአማራ ወጣቶች በአማራነታችን የምንደራጀው ከአማራው ባሻገር ለኢትዮጵያዊነት የከፈሉት መሥዋዕትነት በያ ትውልድና ተከታዮቹ እንደ ክህደት ተቆጥሮ፣ አንሶና ታሪካቸው ተዛብቶ «ጎበና» እየተባሉ እንዲሸማቀቁ ለተደረጉትና ድምጻቸው እንዳይሰማ ለታፈኑት አያሌ እውነተኛ ኢትዮጵያውያንም ድምጽ ለመሆን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *