ስለ አማራ መደራጀት -ክፍል ፫

በአቻምየለህ ታምሩ፡

አማራ አገር አጥፊዎቹ ኮምኒስቶችና ዘረኞቹ ብሔርተኞች የጣሏትን አገርና ወና ያስቀሯትን ኢትዮጵያን ለመጠገን ያጠፋውን ጊዜና ገንዘብ በሚገባ ቢደራጅበትና ቢንቀሳቀስበት ኖሮ እንዳለው ከፍተኛ እምቅ ኃይል መጠን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር የለውጥ ማዕበል ማስነሳት በቻለ ነበር።

ለምሳሌ በ2016 በዓለም ባንክ ዘገባ መሠረት ኢትዮጵያ 3.7 ቢሊየን ዶላር remittance ያገኘች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60 ፐርሰንቱ ወይም 2.3 ቢሊየን ዶላሩ ያማራ ልጆች የላኩት ነው። ይህ የአማራ ልጆች ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩት ገንዘብ ግን የሚገባው በወያኔዎች እጅ ነው። ይህ ማለት የአማራ ልጆች ወያኔ 2.3 ቢሊዮን ዶላር በየአመቱ እንዲዘርፍ ይተባበሩታል ማለት ነው።

ይህ ገንዘብ ኢትዮጵያ በብር የምትበጅተውን አመታዊ ባጀት ከ30 በመቶ በላይ የሚሸፍን ሲሆን ሀገሪቷ በጠቅላላው ከexport ከምታገኘው ዓመታዊ 3 ቢሊየን ዶላር በ700 ሚሊዮን ዶላር ይበልጣል።

ስለዚህ አማራ ዶላሩን ወደ ሀገር ቤት በመላክ አማራን የሚገድሉ የትግራይ ሽፍቶችን ከሚያበለጽግ አማራው በብዛት በሚኖርባቸው በምዕራብ አገራት ገንዘቡን ማንም በማይቀልብበት ሁኔታ ተደራጅቶ ጠንካራ ተቋም በመመስረት ውድ ገንዘቡን አንድ ላይ በማሰባሰብ በዓለም ዙሪያ አዋጭ በሆኑ ሴክተሮች ላይ invest ቢያደርግ አይደለም ኢትዮጵያን ዓለምን የአማራ ማድረግ ይቻለዋል።

ካወቅንበት 2.3 ቢሊየን ዶላር ከባድ ገንዘብ ነው። አይደለም ይህ ሁሉ ገንዘብ ግማሹ ብቻ እንኳ ባፍሪካ፣ ባሜሪካና ባውሮፓ ትልቅ የንግድ ድርጅቶችን ለማቋቋም ያስችላል። ያንን ስናደርግ ሀያ አምስት አመታት ሙሉ «ወያኔ አትርዱ!» እያልን ስንለምናቸው የከረምናቸው ኮንግረሶችም ሆነ ሰኔቶች ሳንለምናቸው ይሰሙናል።

ለመነሻ ያህል በያመቱ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው የንግድ ተቋም በመክፈት ወይም በመግዛት መጀመር እንችላለን። ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖር አንድ ሚሊዮን አማራ አንድ ሺ ዶላር አንዴ ቢያዋጣ አንድ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ማዋጣት ይችላል። ክብር ለጀግኖች አያቶቻችን ይሁንና መልካምና ስምና ዝና ትተውልን ሄደዋልና ለኛ ባያቶቻችን ለምንኮራ ኢትዮጵያውያን ብዙ የአለም አገሮች ካልተነካው ሀብታቸው ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ለኢትዮጵያውያን የመዋለ ንዋይ ፈቃድ ለመስጠት አይናቸውን አያሹም። ባለጌው መለስ ዜናዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባቆሙት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ «አድሀሪ»ብሎ በመሳደቡ የተናደዱት አፍሪካውያን እውነተኞቹን የቀ.ኃ.ሥ. ልጆች አይደለም ለመዋለ ንዋይ ለጉብኝት እንኳ ብንሄድ በቀይ መንጣፍ ነው የሚቀበሉን።

መላው አለም ላለፉት አርባ ሁለት አመታት የጥቁሮች የተስፋ አርዓያ ስለሆነችው ኢትዮጵያ ሲሰማ የኖረው ካዋረዷት ከወታደሩ መንግስቱ ኃይለ ማርያምና ከሽፍታው መለስ ዜናዊ ብቻ ነው። እኛ ባያቶቻችን የምንኮራ ኢትዮጵያውያን በጀግኖች አያቶቻችን ተጋድሎ የምንኮራ ኢትዮጵያውያን መሆናችንን በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና መነሻነት፤ በባንዲራችን ምልዕክትነት ከቅኝ ግዛትና ከባርነት ለተላቀቁ እውነተኛ የአፍሪካ ልጆች መናገር መጀመር አለብን። እስካሁን የአያቶቻንን መልካም ስምና ዝና አልተጠቀምንበትምና ጀግኖቹ አያቶቻችን ባይበገሬነት መንፈሳቸውና በማይከጅሉ እጆቻቸው ሰርተው ትተውልን በሄዱት መልካም ስምና ዝና የአብዛኞቹን የአለም ሀገራት በር አንኳኩተን ልናስከፍትበት ይገባል።

ስለዚህ እውነተኞቹ የአያቶቻችን ልጆች የሆንን ኢትዮጵያውያን እንዳለን ዓለም በሚግባ እንዲያውቀንና አገራችንን ከፋሽስት ወያኔ ነጻ እንድናወጣ በፖለቲካ ከመደራጀት ጎን ለጎን የቢዚነስ ኢምፓየር መፍጠር አስፈላጊ ነው። ከኛ በአምስት እጥፍ የሚያንሱት አይሁዶች ከሰሩት እኛ ከነሱ አንድ አምስተኛ የሚሆነውን መስራት አያቅተንም። ለፖለቲካው ትግል መቃናት የኢኮኖሚ አቅም ወሳኝ ነው። ወያኔ የሚገድልብንን አንድ ሰው ለማሳከም gofundme እያልን ጉዳተኛ እስኪሞት ጊዜ ከምንፈጅ የቆሰሉትንም ጤነኞቹም ተጠቃሚ የሚሆኑበት የአማራ የቢዝነስ ኢምፓየር ማቋቋም አለብን።

አንድ የዓለም አቀፍ ህግ አለ። ሀገራት ለራሳቸው ሲሉ አሉ ከተባሉ የቢዝነስ ተቋማት መሪዎችና ወኪሎቻቸው ጋር ይነጋገራሉ። ዋናው የካፒታል አቅም ፈጥሮ አለ የሚባል የአማራ የቢዝነስ ተቋም መፍጠር ብቻ ነው እንጂ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንችላለን። አንድ ቢሊዮን ዶላር ካፒታልና ከጀርባው ሀምሳ ሚሊዮን ህዝብ ያለውን ድርጅት የማያናግር ያገር መሪ የለም። ይህ የአሜሪካ መሪዎች ይጨምራል። አያቶቻችን ሲተርቱ «ወርቅ የጫነች አህያ የማትገባበት የለም» ይሉ የለ! ታዲያ ተረቱን ለወሬ ማጣፈጫ ብቻ ሳይሆን ኮስተር ብለው በተግባር ልንጠቀምበት ይገባል።

ያኔ የኢኮኖሚ አቅማችን ይፈረጥማል! የኤኮኖሚ ጡንቻችን ሲፈረጥም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በበጎ ጎን የመለወጥ እድላችሁም የሰፋ ነው። ስለዚህ ሁላችን ጥረን ለፍተን ያገኘናትን ዶላር ወደ ወያኔ እየላክን ኢትዮጵያን ከምናዘርፍና ለዚያ ገበሬ የሽንኩርትና በርበሬ መግዣ እንኳ ሳንተርፈው ከምንቀር ትልቅ ቁም ነገር እንስራበት።

ለዚህ ተፈጻሚነት የድርጊት መርሀ ግብር በመንደፍ በኤኮኖሚክስና በተለያዩ ተዛማጅ የትምህርት ሙያዎች እውቅ የሆኑና በታዋቂ የምዕራብ የትምህርት ተቋም ውስጥ የሚሰሩ አማራ ኢትዮጵያውያንን ተነሳሽነቱን ወስደውና መንገድ ፈልገው ውይይት በመጀመር የማህበረሰብ አለኝታነታቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው። በቢዝነስ ህግ የሚተዳደር ታላቅ የአማራ የቢዝነስ ኢምፓየር/ተቋም ንድፍ ጭንቅላታቸውን ጨምቀው ማዘጋጀት አለባቸው። አይሁዶች የተከተሉት ይህንን ተመሳሳይ መንገድ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *